ሁነኛ መሪ ያላገኘው የሕዝብ አመፅ

ልዑል

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አመፅ፤ ሲተሻሽ፤ ሲታመስ ፤ -ሲብላላ ሲቁላላ ፤ ከቆየ በኋላ ፤ ከጥቂት ወራት ወዲህ፤ በየቦታው እየፈነዳ በመቀጣጠል ላይ ይገኛል። የተዳፈነ እሳት የጠፋ መስሏቸው ሲዝናኑ የነበሩት ዘረኞቹም፤ ዛሬ፤ የሚይዙት- የሚጨብጡት አጥተዋል። ወዎያኔዎቹ አመፁን ለመግታት የሞት – ሽረት ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውም እየታየ ነው ። ምዕራባውያን አለቆቻቸውም፤ የአልጋ- ቁራኛ ሆኖ የሚጠራሞተውን ዘረኛ አገዛዝ፤ የህይወት እስትንፋስ ለመስጠት በመሯሯጥ ላይ እንደሆኑ ተደርሶባቸዋል። የሕዝቡን አመፅ ለማኮላሸት፤ በሙያው የተካኑ ባለሙያዎችም ሰሞኑን ወደ አዲስ አበባ መላካቸው ያደባባይ ምሥጢር ሆኗል ። አንድ የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ( ስቴት ድፓትርመንት ) ረዳት ምኒስትር አዲስ አበባ ሄዶ ከወያኔ ባለስልጣኖች ጋር ተነጋግሮ ተመልሷል ። አሜሪካ፤ በኢትዮጵያ የተነሳሳው አመፅ በብርቱ እንዳሳሰባት፤ ለወያኔዎቹ ነግሯቸዋልም ተብሏል። ” ካላወቃችሁበት ፤ ጥቅማችንን ለማስጠብቅ የሚያስችለንን ርምጃ እንወስዳልን ” ሳይላቸው እንዳለቀረ ይገመታል።  ‘ ብታውቂ እወቂበት ፤ እኔ አላውቅልሽም ፤  ጥቅሜን የሚያስጠብቅ ሌላ አሽከር አላጣም ! ”  ” ቋሚ-ዘላቂ ጥቅም እንጅ፤ ቋሚ- ዘላቂ ወዳጅ የለም ” ተብለዋል ወያኔዎቹ፡፡ በመሠረቱ የተበላሸውን ተስፋ-ቢስ አገዛዝ በሽታ ፤ እንኳንስ ከውጭ በመጣ ወጌሻ ይቅርና፤ በማነኛውም የቀድዶ -ጥገና ህክምናም ቢሆን ሊድን አይችልም። ይህ ዘረኛ አገዛዝ የአሳ ግማቱ ከጭንቅላቱ እንደሚባለው የበሰበሰው ፤ ከራሱ ካናቱ፤ ስለሆነ፤ መዳኛ የለውም። የማይድን በሽታ ደግሞ ፤ ከነበሽተኛው ወደ ከርሰ-መቃብር መሸኘት ነው ያለበት! አብዛኛው ሰው ያልተረዳው ነገር ቢኖር፤ የሀገራችን ስር የሰደደ ችግር ፤ እንኳንስ የውጭ ዜጋ ቀርቶ እኛው እራስችንም ብንሆን መፍትሄውን፤ እስካሁን ልናገኘው አለመቻላችንን ነው ። እንደ አባይ-ጠንቋይ ፤ ሞራ- ገልባጭ፤ እንደ አፈረሰ ደብተራ መጽሐፍት- ገላጭ፤ እንደ ንጉሥ ባለሟል ዋንጫ -አቅራቢ፤ እንደ ፊውዳል አጋፋሪ ሠልፍ አሳማሪ- ከመሆን ያለፈ ተግባር መፈፀም አልቻልንም። ባጭሩ፤ እስካሁን ድረስ፤ ወያኔን የሚያስደነግጥ የረባ ተግባር አልተፈፀመም ነው መልዕክቱ ! ወያኔ፤ ተቃዋሚውን ሁሉ ለመግደል ፤ ልክ ዶሮ ከማረድ የበለጠ ቀሎለታል ። አንድ ያልተገነዘበው ጉዳይ  2 ቢኖር ግን፤ ምን ጊዜውም ቢሆን ፤ የሰው ልጅ ደም ፤ እንዲሁ በከንቱ ፈስሦ ሊቀር የማይችል መሆኑን ነው ። ደም አይደርቅም ። የሰው ዘር ፤ ጠፍቶ-አይጠፋም ። ” ምንም ትቢያ ቢሆን አፈሩ ቢያለብሰው፤  መሬት ተቆፍሮ መቃብር ቢውጠው ፤  ስሙ አይቀበርም ልጅ የወለደ ሰው ። ” እንዲሉ፤ የኢትዮጵያም ስም አይቀበርም ! አይጠፋም ! ” ዖ ጊዜ ለኹሉ ! ” እንደተባለው፤ የጊዜ ጉዳይ ነው ! የሕዝቡ አመፅ፤ ከፖለቲካ፤ ከኢኮኖሚና፤ ከማኅበረሰብዓዊ ችግሮች የተወለደ እምቢተኝነት ነው። የአልገዛም ባይነት የመጨረሻውን ደረጃ ከያዘ ቆይቷል ። እነኝህ ችግሮች የቆዩና የደለቡ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ” ከዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ” እንዲሉ፤ አሁን ደግሞ፤ ዘረኝነት የሚባል አዲስ በሽታ መጥቶ፤ የቆየውን የሀገራችን ችግር በይበልጥ አባብሶታል ። የችግሮቹ መደራረብና መከማቸት፤ ሕዝባዊ አመፁን በይበልጥ መራራ አድርጎታል። አመፁን ይበልጥ መራራ ካደረጉት ዋና ምክንያቶች አንዱ፤ በአገር-አቀፍ ደረጃ፤ ትግሉን የመምራት ተግባር ደካማ መሆኑ ነው ። ትግሉ አገር አቀፍ መልክ ይዞ ሊመራ አለመቻሉ ደግሞ ፤ የቆየ ችግር እንጅ ፤ አሁን የተከሰተ አይደለም ። ከዚህ ኮፈን በግድ መውጣት አለብን ። ያለዚያ፤ የዘር ፖለቲካ በሀገራችን ስር እየሰደደ እንዲሄድ መፍቀድ ይህናል ፡፡ ይኸ ደግሞ ፤ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር፤ ሕዝቧም እንደ አንድ ሀገር ዜጋ እንዳይኖሩ ማደርግ ነው ። ይኸ ለማንም አይበጅም ! እኛ አጥፊና ጠፊዎች ከሆን፤ ተጠቃሚ የሚሆኑት የሀገራችን ጠላቶች ብቻ ናቸው ። ጠላቶቻችን ማን እንደሆኑ ስለሚታወቁ ፤ እነርሱን መጥቀስ ፤ ለእነርሱ ክብር መስጠት ይሆንብናል ። ከአለፉት አምሳ ( 50) ዓመታት ጀምሮ ኢትዮጵያ፤ ጀግና እንዳታገኝ፤ ሀገር-ወዳድ እንዳይወጣ፤ ለሕዝብ ቀናኢ የሚሆን ወጣት ትውልድ እንዳይበቅል፤ ምሁር እንዳይኖር፤ ታጋይ ኃይል እንዳይበረክት፤ ሆን ተብሎ በስፋት ሲካሄድ የነበረ ዘመቻ ውጤት ነው ። ለዚህ አጥፊ ዘመቻ፤ ደርግ የበኩሉን ወንጀል ፈጽሞ ሄዷል። ያ አስከፊ ቁስል ለመሻር በሚጣጣርበት ጊዜ ደግሞ ፤ በወያኔ የዘር ጥላቻ መርዝ ፤ ሕዝብ የአብሮነት ዕድሉ እየተዘጋበት ነው። በዚህ አሳዛኝ ሁኔታ፤ በሀገር ደረጃ እንዴት መሪ ማውጣት ሳይቻል ቀረ? ይህ፤ የሁሉ ዜጋ ጥያቄ ከሆነ ቆይቷል ። በሀገራዊ ደረጃ ትግሉን አስተባብሮ እንደመምራት ሁሉም በየበኩሉ የየአካባቢው አውራ ለመሆን ይፎካከራል። እርስ በእርሱ ይነታረካል ። በአንድ ዓላማና ራዕይ ዙሪያ ሆኖ ለመሪነት መወዳደሩ ባልከፋም ነበር። እንዲያውም የሚደገፍና የሚበረታታም ነው። ያ ሳይሆን እየቀረ፤ ዛሬ፤ ሀገሪቱ ወደ- ዘመነ መሣፍንት ግዛት እየተሸጋገረች ነው ብሎ የሚሰጋው ሕዝብ ቁጥር በቀላል የሚገመት አልሆነም። ቅድሚያ ለጎሳዬ፤ ትኩረት ለብሄሬ፤ ጭንቀት ለመንደሬ፤ የሚለው የዘረኝነት ልክፍት፤ የሀገራችንን ፖለቲካ መልከዐ- ምድር በክሎታል። ይህ ደግሞ የወያኔ የጎሣ ክልል የረጭው መርዝ ነው። ይህን የተበከለ ( polluted ) አየር ማስወገድ የሚቻለው፤ በሀገር -አቀፍ ደረጃ ማሰብና መደራጀት ሲቻል ነው።  3 በዕርግጥም፤ እነኝህ ኃይሎች አንድ ላይ ተስባስበው ኅብረት መፍጠር ከቻሉ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሀገራችንን ፖለቲካዊ መልከዐ- ምድር፤ ጥራት ባለው መልኩ መለወጥ ይቻላል። ዛሬ የሚያስፈልገን ለውጥ፤ የጥራት- የዓይነት(QUALITY ) ነው እንጅ ፤ የይስሙላ ለውጥ፤ የጥግና ለውጥ፤ የጉልቻ ለውጥ አይደለም። አዲሱን ወይን በአሮጌ ስልቻ፤ ቢያስገቡት፤ ስልቻው ይቀደዳል ወይኑም ይፈስሣል። ሊጠጣ የተዘጋጀውም ፤ አፉን ክፍቶ ይቀራል ። በኢትዮጵያ የሚጠበቀው ለውጥ፤ መሠረታዊ ለውጥ ነው ። የሥርዓት ለውጥ ! ይኽ ማለት ፦ 1ኛ. የፖለቲካ ሥርዓት ለውጥ ፦ በዘር ላይ የተመሰረተው አገዛዝ ከህገ መንግሥቱና ዝባዝንኪው ጋር በኢትዮጵያ ዳግም እንዳይንሰራራ መውገድ አለበት። የዘር ፖለቲካ በሀገራችን ወደፊት ቦታ አይኖረውም። ለሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን አስተሳስብ፤ አጅግ ኋላ ቀር የሆነ አመለካከትና የሥልጣኔ ተቃራኒ ነው ። በሀገራችን ሕዝብ በኩል ተቀባይነት የሌለውና ተተፍቶ የተጣለ ነው። 2ኛ. የኢኮኖሚ ሥርዓቱ ከዕዝ ቁጥጥር ነፃ ሆኖ፤ የግል ሀብትና ይዞታን መብት የሚያስከብር ሊሆን ይገባል። አብዛኛው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የተመሰረተው በግብርና ላይ በመሆኑ፤ መሬት የግል ባለቤትነትና ተጠቃሚነት በህግ መከበር እንዳለበት አያጠያይቅም። እረ ለመሆኑ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በገዛ ሀገሩ መሬት ላይ ባለቤት፤ አዛዥና ተጠቃሚ ካልሆነ፤ ሌላ ማን ሊሆን ይችላል ? 3ኛ. የሀገሪቱ የውጭ ፖሊሲ/አመራር ገለልተኛና አዎንታዊ ( Positive Neutrality) መሆን አለበት። የኢትዮጵያ የውጭ ፖሊሲ፤ ለማነኛው ባዕድ ኃይል ተቀጽላ፤ የተኮደኮደ፤ ተሸማቃቂና ደንገጥር ሊሆን አይገባውም ። በሕዝብ የተመረጡ የሀገር -ቀናዒ መሪዎች ከመጡ፤ ይህ ሊሆን አይችልም። አዎንታዊ ገለልተኝነት ሲባል፤ ሀገራችን፤ ብሄራዊ ጥቅሟን ለማስከበርና ለመጠቀም፤ ከማነኛውም ክፍለ -ዓለም ካሉ ሀገሮች ጋር ወዳጅነቷን ለመመስረት የሚያስችላትን ምርጫና ነፃነት እያስከበረች ትቅጥላለች ማለት ይሆናል ። ከየትኛውም ቡድን ( Blok ) ጋር፤ እንደ አስፈላጊነቱ ወገንተኛ መሆን ወይም አለመሆኗ ፤ የራሷ – የግሏ ውሳኔና ምርጫ ይሆናል ። ከውጭ ለሚገኝ/ ለሚመጣ ርዳታ ተብሎ፤ በሉዓላዊነቷ ላይ አትደራደርም። በጭብጥ ምሥር ብኩርናውን አትለውጥም ማለት ነው ። ይህ የነጠረ የውጭ ፖሊሲ አመራር መርኋ ፤ በዓለም አቀፍ መድረኮች ሁሉ ተከባሪነትንና አመኔታን ያተርፍላታል ብለን እናምናለን ። 4ኛ የብሄራዊ መከላካያ ኃይል / ሠራዊት፤ ተጠያቂነቱ፤ ኃላፊነቱና ታማኝነቱ ፤ በኢትዮጵያ ሕዝብ በ/ለተመረጠ ምክር ቤት ( ፓርላመንት ) ብቻ ይሆናል ። ለ/ ከማንም ፓርቲና ፖለቲካም ሆነ ቡድን ጋር ሊወግን አይፈቀድለትም ። ከማንም ብኄር- ፖለቲካ- ኢኮኖሚና ሃይማኖት ቡድን ጋር ግንኙነት አይኖረውም ። አመሰራረቱ – አወቃቀሩ ፤ ሥልጠናው ፤ ወታደራዊ ርዕዮቱ ( Military Doctrine ) ሙያውና ተልዕኮው፤ ታማኝነቱና መሥዋዕትነቱ ሁሉ ሲጠቃለል፤ የኢትዮጵያን ሀገራዊ ነፃነትና ሉዓላዊነት መጠበቅ ይሆናል። የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ሀብትና አቅም በፈቀደው መጠን፤ ተደራጅቶና ታጥቆ ፤ ግዴታውን ይወጣል ። አልኝታውን ያስመስክራል። ዋስትናውን ያረጋግጣል ።  4 ምን ጊዜም ቢሆን፤ ከእንግዲህ ወዲህ፤ የመከላካያ ሠራዊቱን በትኖ፤ ሀገሪቱንም ለአደጋ አጋልጦ የሚሸሽ መሪ፤ ኢትዮጵያ ወስጥ አይፈጠርም ! ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፤ ራሱ የሀገሩን ሉዓላዊነት አስከብሮ፤ የህግ የበላይነት ሲያረጋግጥ ብቻ ነው ። 5ኛ. የኢትዮጵያ ሀገራዊ ኅልውናም ሆነ የሕዝቧ አንድነትና አብሮነት፤ “ሰማይ ዝቅ ፤ መሬት ክፍ ” ቢል፤ ከጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም። ይህ ጉዳይ፤ የመፈክር ቃል- አግንኖ ሳይሆን ፤ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ከስጋውና አፅሙ፤ ከደሙና ኅዋሳቱ ፤ ከመንፈሱና ኅላዌው ጋር ተቆራኝቶ የኖረና የሚኖር እውነታ ነው። እያንዳንዱ ዜጋ የኑሮውና ኅልውናው መግለጫ ፤ የሀገሩ መኖር-አለመኖር በመሆኑ፤ እንደማነኛቸውም የዓለም ሕዝቦች ሁሉ ፤ እኛም ኢትዮጵያውያን መኖር ስለአለብን ፤ የምንኖርባት ኢትዮጵያም ዘለዓለማዊ ሆና እንድትኖር እንፈልጋለን። ሌላም ምርጫ ሊኖርን አይችልም ። ኢትዮጵያን እንደ አማራጭ ከሚያዩዋት ወያኔና መሰለቹ ጋር ያለን ልዩነትም ከዚህ መሠረታዊ ዕምነት የመነጨ ነው። ከላይ፤ ከአንድ እስከ አምስት ተራ ቁጥሮች የተዘረዘሩት መሠረታዊ መርኆዎችና ሀገራዊ አቋሞች ልዩነት ምክንያት ከወያኔ ጋር፤ በአጥፊና – ጠፊ ጎራ እንድንሰለፍ ተግድደናል ። ይኽ የማይታረቅና የማይቀራረብ አቋማችን ለድርድር ሊቀርብ አይችልም። በ 1981 ዓም የሎንዶን ጉባዔ ልንሳተፍ ያልቻልነውም በዚህ ምክንያት ነው። ኢትዮጵያዊ ማንነታችንን፤ የወያኔ አለቆች፤ ሄርማን ኮኽንና Herman Cohen ፖል ሄንዝ Paul Hanze በሚገባ ስለተረዱት በጉባዔው እንድንገለል ተደረገ ። የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ከሚባሉት መካከል በመጀመሪያው ረድፍ ላይ በመገኘታችንም፤ ለፅናታችን ይበልጥ ጥንካሬ አንዲኖረን አድርጎናል ። ሀገራችን፤ በረዥም ዘመናት ታሪኳ ሂደት፤ የተለያዩ አስቸጋሪ ፈተናዎች እየገጠሟት ሁሉንም እንደ አመጣጣቸው ተቋቁማ ፈተናዋን አልፋለች። አብዛኛዎቹም በኅልውናዋ ላይ ያነጣጠሩ ነበሩ። ኩሁሉም የከፋ የኅልውና ፈተና የገጠማት ፤ በአሁኑ ወቅት እንደሆነ ሁሉም ይስማማበታል። የዛሬውን ፈተና ፤ እጅግ የከፋ የሚያደርገው ፤ አደጋውን ያመጡት ፤ የውጭ ባዕዳን ወራሪ ኃይሎች ሳይሆኑ፤ ሀገር – በቀል የሆኑ ከሃዲዎች በመሆናቸው ነው። እንደ ውጭ ወራሪ ኃይል ተቆጥረው፤ ሕዝቡ የውጭ ዕርዳታ ሊጠይቅ በማይችልበት አኳኋን በመሆኑ፤ ሁኔታው የተወሳሰበ እንዲሆን ሆኗል ። ይህንን ዕንቆቅልሽ በመፍታት፤ የጋራ ራዕይና ስልት ቀርፆ፤ አመራር መስጠት የሚችል ሀገራዊ የጋራ ኃይል ባለመኖሩ፤ ችግሩን ይበልጥ ውስብስብና ጥልፍልፍ እንዲሆን አድርጎታል ። ኢትዮጵያውያን ምሁራንም፤ ይህንን በሚመለከት፤ የጋራ ብሄራዊ ሠነድ ሊያቀርቡ አልተሳካላቸውም ። ሀገር ወዳድና ለሕዝብ ቀናኢ የሆነ ምሁር ያልተሳተፈበት ብሄራዊ የነፃነት ትግል ደግሞ ብዙ ነገር ይጎድለዋል ። በታጋይ ድርጅቶችና በሀገር ወዳድ ምሁራን መካከል ያለው ክፍተት እስካሁን ድረስ ሲሰፋ እንጅ ሲጠብ አይታይም ። የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት፤ እስካሁን የጠቀመው፤ ወያኔንና ባዕዳን ብቻ ለመሆኑ፤ የሚካድ አይደለም ። ይህን ችግር በአግባቡ የተገነዘቡ ክፍሎች ካሉ ፤ በብርቱ ሊያስቡበት ይገባል ። አሁን የፈነዳው ሕዝባዊ አመፅ፤ ጣምራ ዕድሎችን አምጥቷል ማለት ይቻላል ። እነኝህ ጣምራ ሁኔታዎች እንዳያመልጡ ከተፈለገ፤ በአግባቡ ተጠቅመንባችው ሀገራችንን ከገባችበት ማጥ ልናወጣት 5 ግድ ይሆንብናል ። ሀገሪቱም ከምን ጊዜውም በበለጠ ዛሬ መስቀለኛ መንገድ ላይ ትገኛለች። ሁለት ምርጫዎች ተደቅነውባታል ። 1ኛ. ሀ. ሕዝባዊ አመፁን፤ በሀገር-አቀፍ ደረጃ አስተባብሮ በመምራት ፤ ለድል የሚያበቃ የጋራ አመራር ፈጥሮ መንቀሳቀስ፤ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም። ። ይህን ዕድል መፍጠር ከተቻለ፤ ሀገሪቱን ወደ ብሩኅ ተስፋ የምታመራበት በር ይከፈታል ። ሀገራዊ ኅልውናዋም ይረጋገጣል ።  ለ. ወያኔ ከነ አጥፊው ዘረኛ አገዛዙ ይወገዳል። ይህ ካልሆነ ፤ ሊከሰት የሚችለው ስጋት ሁለተኛው ሊሆን ይችላል ብሎ ማሰብ ይገባል ። 2ኛ. በየቦታው ለሚንቀሳቀሱ የጎበዝ አለቆች፤ የትግሉን ሜዳ አስረክቦ፤ ሀገሪቱን፤ ወደ ማያባራና ማንም ኃይል ሊቆጣጠረው ወደ ማይችል የእርስ- በእርስ ፍጅት ማምራት ይሆናል። ይህ ሊሆን አይችልም ብሎ መዘናጋት ፤ ኃላፊነት የጎደልው ብቻ ሳይሆን፤ ሀገሪቱ እንድትጠፋ እንደመተባበርም ይቆጠራል ። በአሁን ጊዜ፤ በኢራቅ፤ በሦርያ፤ በየመን፤ በሊቢያና በመጠኑ ቢሆን፤ በቱኒዚያ እየሆነ ያለውን የሚመለከት ሰው፤ ኢትዮጵያን አይነካትም ብሎ ሊዘናጋ አይቻለውም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ፤ ለአለፉት ግማሽ ምዕተ-ዓመታት ፤ ለዴሞክራሲ ሥርዓት መልካም አጋጣሚዎች እየመጡለት ፤ ሳይተቀምባቸው እንዲሁ በከንቱ አልፈውበታል ። በእጁ ካስገባቸው በኋላ አምልጠውታል ። የሥልጣን ጥመኞችና አፍራሽ ኃይሎች ነጥቀውታል ። ተስፋው ተዳፍኖበታል ። አሁን ያለበትን ሁኔታ እርሱ ባለቤቱ ፤ ማንም ሳይነግረው ያውቀዋል ። በሁኔታው ውስጥ እየኖረ ስለሚኖር ፤ ያንን ዝርዝር ማንም እንዲነግረው አይሻም። ቁስሉን የሚሽርለት እንጅ ሰቆቃውን የሚያስታውስው አይፈልግም። ረሃብ -ጥማቱን የሚያስወግድለት እንጅ፤ ስለ ረሀብ-ጥማቱ የሚያስታውስው አይፈቅድም ። ” የአዛኝ ቅቤ አንጓች ” መወድስ አይፈልግም ። ይኽ ፤ የሕዝብ እንቅስቃሴና አመፅ ሁነኛ መሪ አላገኘም ። ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ፤ ምናልባት ግቡን ላይመታ የሚችልበት ዕድል ሊያጋጥመው ይችል ይሆናል ። አሁን እንደሚታይው ከሆነም፤ ወያኔዎቹና አለቆቻቸው ተባብረው አመፁን ሊያኮላሹት ይመኛሉ። አቅጣጫውንም አስቀይረው እነርሱ ወደሚፈልጉበት ግብ እንዲሄድላቸውም ጥረት ያደርጋሉ ። ይህ ከተሳካላቸው የተመኙትን እንደሚያገኙ ማንም ሊጠራጠር አይገባውም ። ታዲያ እነርሱ ” እንደ ተመኛኋት ይኸው አገኘኋት ! ” ሲሉ፤ እኛ ደግሞ ፤ ለሚቀጥለው ሠላማዊ ሠልፍ እንዝጋጃለን ። ” ግመሎቹ ሲራመዱ፤ ውሾቹም ይጮሃሉ ! ” ተብሏልና ! ይኽ ክስተት ከመምጣቱ አስቀድሞ፤ የአንድነት ኃይሉ፤ በአስቸኳይ ተጠራርቶ በጋራ እንዲቆም የማይታክተውን የዘውትር ጥሪ አናስተላልፋለን !

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s