woyane -woyane new-

ወዳጅን ቢከፋውም ጠላት ግን ደስ ይበለው – ሀገራችን በአሁኑ ወቅት ለይቶላት ጨርቋን ጥላ ዐብዳለች፡፡ ዕብደት እንዴት ይገለጻል? የሀገርና የሕዝብ ዕብደት እንደኔ አስተሳሰብ በሚከተሉት ሁኔታዎች ሊገለጽ ቢችል የሚያስማማ ይመስለኛል፡፡ የዋጋ ንረቱን ስንመለከት ከምክንያትም ከሰብኣዊነትም በእጅጉ ያፈነገጠ ነው፡፡ የሁሉም ነገሮች ዋጋ የሚወሰነው በሕግና በሥርዓት ሣይሆን በሻጮች አላግባብ የማደግና የመበልጸግ ፍላጎት ብቻ ነው፡፡ ገበያውን ሃይ የሚል መንግሥታዊ ተቋምም ሆነ ሕግ በጭራሽ የለም፡፡ ኅሊና ከአናት ወርዶ ቦርጭ ውስጥ ከተሸጎጠ እነሆ በትንሹ 11 ዓመታት ሆነው፡፡ ከ97 ምርጫ ወዲህ የወያኔው መንግሥት በተለይ የአዲስ አበባን ባጠቃላይ ደግሞ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመበቀል በቀየሰው አዲስ የአገዛዝ ዘይቤ ሕዝብን በኑሮ ውድነት መቅጣቱን በስፋትና በጥልቀት ተያይዞታል (በፈለጉት መንገድ ገንዘብ ስለሚያግበሰብሱ ይህ ብቀላ ወያኔው “የኔ ናቸው” የሚላቸውን ወገኖች እንደማይነካቸው ግልጽ ነው፤ ከዕድር ቤት ጠባቂነት በጥቂት ዓመታት ውስጥ ባለአምስት የአንደኛ ደረጃ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ባለቤት የሆነው ሰሜነኛ ወንድሜ – ለደኅንነቱ ስል ስሙን የቀየርኩለት – ሐጎስ ለዚህ ምሥክር ነው)፡፡ በመሆኑም የማንኛውም ዕቃና አገልግሎት ዋጋ ወደ ሰማየ ሰማያት ሲወነጨፍ ከዝምታና ምናልባትም ችግሩን ይበልጥ ከማወሳሰብ ውጪ በያገባኛል ስሜት ለሕዝብ ተቆርቁሮ የወያኔው በድን ማለትም ቡድን ዋጋን ሲያረጋጋ አልታየም፤ ወደፊትም በርግጠኝነት አይታይም፡፡ ሀገሪቱ በኳስ ዐበደች የለዬለት የጨረባ ተዝካር ውስጥ ልትገኝ የቻለችው እንግዲህ ቅንቅናም እንጂ ቅን መንግሥት ባለመኖሩና የመንግሥት ተብዬው ባለሥልጣናትም በንግዱ ውስጥ ገብተው ከነጋዴው ጋር አብረውና ተባብረው ስለሚዘርፉ ነው፡፡ በደመወዙ ብቻ የሚኖር ባለሥልጣን ቢገኝ ከምላሴ ፀጉር ይነቀል፤ ጭራሽ አይታሰብም፡፡ ለዚህም ነው ለመንግሥት ሠራተኞች ማሻሻያ ቢደረግ ባይደረግ ጉዳያቸው ያልሆነው፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ሆኑ ነጋዴው ከፈሪሃ እግዚአብሔር መንገድ ወጥተው፣ ኅሊናቸውንም ለገንዘብና ለጌታቸው አያ ሣጥናኤል ሸጠው ሕዝብን በጭካኔ እየዘረፉ ራቁቱን አስቀርተውታል፡፡ የኔን መሰሉ ደህና የሚባል የአንድ ወር ደመወዝ ከሦስት ቀናት በዘለለ አያኖርም (አምስት ሺ ብር ምን አላት? ለአለቃየ እኮ የሣሎን ውሻውና የውርዬ የወር በጀት ናት!)፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ካልዘረፍክና ካልሰረቅህ ወይም በሙስና ተዘፍቀህ ብዙ ገንዘብ ካልመዘበርክ መኖር አትችልም – በጥኋራ ገቢህ ቤት ለመሥራት ማሰብ ዕብደት ነው፤ ልብስና ጫማ መለወጥ ራሱ ህልም ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ እኮ እኮ ሸሚዝ ለመግዛት ዕቁብ እየገባን ነው፡፡ ዱሮ የገዛነውን ጫማ ለማስጠገን ብቻ ዱሮ ጫማውን ከገዛንበት ዋጋ ከዕጥፍ በላይ እንጠየቃለን፡፡ በዘንድሮ ጫማ ማስጠረጊያ ዱሮ ሁለት ጫማ ትገዛበት ነበር – እያጋነንኩ እንዳይመስልህ፤ በፍጹም አይደለም – ፒያሣ ሂድና አስጠርግ – ከጎንህ ታገኛታለህ፡፡ ግን ሙስና የመንግሥትም ሆነ የግል ተቀጣሪ ሠራተኞች የዕለት ከዕለት እስትንፋስ በመሆኗ ይህ የምለው የኑሮ ውድነት እኔን መሰሉን ከርታታ ዜጋ እንጂ ሙሰኛውን አይመለከትም፡፡ ሰው ገድለህ ብትታሰር ከ10 እስከ 20 ሺህ ብር ጉቦ ከፍለህ ፋይልህን ማስጠፋትና ነፃ መውጣት “መብትህ” ነው፡፡ በየመሥሪያ ቤቱ ስትሄድ ፋይልህን ከመጥፋት ለማዳን ወይም የባላንጣህን ፋይል ድራሹን ለማስጠፋት ኪስህን ተማምነህ ብትሄድ በቀላሉ ይሳካልሃል፡፡ “ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ” ማለት በዚህን ዘመን ነው፡፡ የፖለቲካ አይሁን እንጂ ማንኛውንም ዓይነት ወንጀል ሠርተህ ገንዘብና ጠብደል የወያኔ ባለሥልጣን ዘመድ ካለህ ግፋ ቢል ለጥቂት ሰዓታት ወይም ቀናት ብትታሰር እንጂ ተሸቆጥቁጠው ይፈቱሃል፡፡ የወያኔው አባልና የዘር ሀረግ ከሆንክ ደግሞ ወንጀል መሥራትና መሞሰን መዝናኛዎችህ እንጂ የሚያስከስሱህና የሚያስቀጡህ አይሆኑም – ለምን ብለው? በጌታዋ የተማመነች በግ ላቷን ቀርቶ ቀፈቷን ውጪ ብታሳድር የሚነካት የለም፡፡ ወንጀለኝነት የሚያሰጋው ድሃውን ነው፡፡ 2 ፍርድ ቤቶችን ስታይ፣ ፖሊስ ጣቢያዎችን ስታይ፣ ሐኪም ቤቶችን ስታይ፣ ቀበሌና ወረዳዎችን እንዲሁም ከፍተኛና ዋናውን የከተሞች መስተዳድር ስትቃኝ፣ ሁሉንም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ስትታዘብ በሁሉም ዘንድ ሙስና የደም ሥር ናት፤ ይሉኝታና አዩኝ አላዩኝ ደግሞ ፋሽናቸው አልፏል – ለትራክ ፖሊስ ባውንድህን መዘህ በግልጽ ስትሰጥ ብትታይ የተበደርከውን ልትመልስ እንዳልሆነ እየታወቀ ሰው ምንም አይልህም – ሙስና ከመለመዱ የተነሣ ዜጎች የሕጋዊነት ያህል ቆጥረው ተቀብለውታል፡፡ የትም ግባ፣ የትም ሂድ ሙስና ባህል ሆኗል፤ ሃይማኖት፣ ይሉኝታና ሀፍረት ሞተው ተቀብረዋል፡፡ ቄሱም ሲሞስን፣ ጳጳሱም ሲሞስን፣ ገበዙም ሲሞስን፣ የደብር አለቃው ሲሞስን፣ ዲያቆኑ ሲሞስን፣ አስኬማውን በወገቡ ዙሪያ አስሮ ሞቱን በቁሙ ያወጀው መነኩሴም ሲሞስንና ሲሸራሞጥ ብታይ የዘመኑን ማብቂያ የሚጠቁሙ መጽሐፍ ቅዱሣዊ ጥቅሶችን በማስታወስ በድንጋጤ ትፈዛለህ እንጂ ሌላ የምትለው ቃል የለህም፡፡ በሙስና ተጠርጥሮ መታሰር ትልቁ የሀገራችን ቀልድ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ ያን የፈረደበት ሙሰኛ ለማሰር የሚጠቁመው ሰው፣ እንዲታሰር ዋራንት የሚቆርጠው ሰው፣ ለማሰር የሚላከው ፖሊስ ወይ ደኅንነት፣ እስረኛውን ተቀብሎ ማረፊያ ቤት የሚያስገባው ሰው … እነዚህ ሰዎች በሙሉ ካለሙስና እስትንፋሳቸው ቀጥ እንደምትል እየታወቀ ሰውን በሙስና ሰበብ ሲያስሩ ስታይ ከመሳቅ ውጪ ምን ልታደርግ ትችላለህ? ወደ ቲያትር ቤትነት የተለወጠች ሀገር ባለቤት መሆንና ከግም ጋር አብረህ መኖርን የመሰለ አስጠሊታና አጸያፊ ነገር ደግሞ የለም፡፡ የት ሄድን እንኑር? ሁሉም ነገር ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ነው፡፡ የፈለግኸው ደረጃ መንጃ ፈቃድ ሕጋዊ መስመርን በተከተለ መልኩ ተሠርቶ እቤትህ ይመጣልሃል – ለየደረጃው የሚከፈለውን ጉቦ ከከፈልክ፡፡ ይህ እንዲያውም በጣም ቀላሉ ነገር ነው፡፡ ገድለህ እንዳልገደልክ በምትቆጠርበትና በሀሰት ምሥካሬ ሟችን እንደገዳይ በምታስደርግበት የበሰበሰች ሀገር ውስጥ መንጃ ፈቃድን በሙስና አውጥተህ በምንትነዳው መኪና በየቀኑ ሕዝብን መፍጀትና ንብረትን ማውደም በጣም “ኅሊናዊ”ና አነስተኛው የሙስና መረብ ነው፡፡ ከዚህ የበላለጡ ደምን የሚያፈሉ የሙስናና ሀገርን የሚያስክዱ፣ ሰው ሆኖ መፈጠርን ሳይቀር የሚያስጠሉ ወንጀሎች እየተሠሩ ነው – ሕግ በጠፋባት ሀገራችን ውስጥ፡፡ ሰውን ግን ምን ነካው? ማሰቢያውን ምን በላበት? ከእንስሳት እንዴት እንነስ? ስንት ሺህ ዓመታትን ለመኖር ይሆን ሰማይና ምድር የማይችሉትን ይህን ሁሉ ወንጀልና ክፋት የምንሠራው? ኧረ አቅል ጀባ ጎበዝ! የነጋዴው ሞራልና ሃይማኖት ደብዛው ከመጥፋቱ የተነሣ የሚሸጡ ዕቃዎች ጥራት እጅግ አሣፋሪና አሳሳቢም ነው፡፡ በልብስና በጫማው ወይም በሌሎች እነዚህን መሰል የማይበሉና የማይጠጡ ዕቃዎች ላይ የሚሠራው ወንጀል ግዴለም ሊባል ይችላል፡፡ ሌላው ሲታይ ግን “ወገን በወገን ላይ እስከዚህን እንዴት ሊጨክን ይችላል?” በሚል ክፉኛ ያስጨንቃል፡፡ ልብ አድርግ – በቅርቡ እንደሰማነው ጀሶን በነጭ ጤፍ እንጀራነት ያቀረቡ ሰዎች አሉ፤ የተወሰደባቸው እርምጅ ካለ አልሰማሁም – ለዚህ ዓይነቱ ወንጀል በኔ ብያኔ በትንሹ ስቅላት ሊሆን ይገባዋል እላለሁ – በተፈጥሮየ ጨካኝ አይደለሁም፤ ግን ይህ ተግባር ከሞትም በላይ ሊያስቀጣ የሚችል ትልቅ ሀገራዊ ወንጀል ነውና ወንጀለኞቹ ሞትም ሲያንሳቸው ነው፡፡ በዘይት ስም፣ በቅቤ ስም፣ በሥጋ ስም፣ በበርበሬ ስም፣ በዳቦ ስም… ሕዝቡን ለበሽታና ለሞት የሚዳርጉ በጣም ብዙ ነጋዴዎች የሚሠሩትን ወንጀል እንሰማለን፤ በመሞትና በመታመሙም እንሳተፋለን – ለነዚህም ዐረመኔ ወንጀለኞች የምሰጠው ብያኔ በትንሹ ስቅላት ነው፡፡ በሙጀሌያም እግር የተረገጠና በአሙካ እጅ የተላቆጠ ሥሪቱ ከማይታወቁ መርዛማ ንጥረ ነገሮች የሆነ “ቅቤ”ና “ዘይት” የሚሸጥ ሰው ቢሞት ዐረም ተነቀለ እንጂ ሰው ሞተ አይባልምና በጭካኔየ አትገረሙ፡፡ ቆዳችን ወፍራም ሆኖ አልሞትንም እንጂ መንግሥትና እሱን የተማመኑ ወንጀለኞች እንዲህ በቁማችን ገድለውናል፤ ንቀውናል፣ አዋርደውናልም፡፡ የሚገዛውን ሕዝብ የሚጠላው መንግሥት ተብዬው የወያኔ ጁንታ ወደ ፖለቲካው አትምጣበት እንጂ እየተበቀለው ያለውን ሕዝብ በዚህ መልክ ብትጨርስለት ሽልማት እንጂ ቅጣት አይጥልብህም፡፡ ዘመኑ ነው፡፡ “ዘመኑ ነው” ብለን ግን ዝም ማለት ያለብን አይመስለኝም፡፡ ከነዚህ በላዔ-ሰቦች ነፃ ለመውጣት ማድረግ የምንችለውን ሁሉ እናድርግ፡፡ 3 በአንዲት ሀገር በትንሹ ሁለት ሕጎች አሉ፤ አንዱ ለድሃው የሚሠራና የማያላውስ ጠንካራው አፓርታዳዊ ሕግ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ሕግ-አልባነት ነው፡፡ የሕግ-አልባነት ሕግና ሥርዓት የሚሠራው ገንዘብ ላላቸውና ለወያዎቹ ለራሳቸው ነው፡፡ ይህ ሕግ ያሻቸውን ነገር ከድሃው ዜጋ መቀማትና መዝረፍ፣ ከቦታና ከእርሻ ቦታዎች መንቀል፣ ማደህየትና ማሳበድ ከሀገርም እንዲሰደዱ ማድረግ የሚያስችል ልዩ ሕግ ነው፡፡ ሀገሪቱ ስላበደች አንድ የ330 ሚ.ሊ ቢራ፣ አንድ ለስላሳ፣ አንድ ሊትር የታሸገ ውኃ ዋጋቸው በአንዳንድ አካባቢዎች ተመሳሳይ ወይም እኩል ነው – እኔ በነበርኩበት አንድ አነስተኛ የገጠር ከተማ እነዚህ ሦስቱ መጠጦች የሚሸጡበት ዋጋ 15 ብር ነው፡፡ በጣም ገርሞኛል፡፡ ውኃው በተለይ ለማሸግ ከሚወስደው የማቴሪያልና የሰው ጉልበት ወጪ በስተቀር ምንም ነገር የማይጨመርበት ሆኖ ሳለ ከቢራ ጋር እኩል መሸጡ የንግዱን የዕብደት ደረጃ ልመዝንበት አስችሎኛል፡፡ ምክንያትና ተጠየቅ (ሎጂክ) ከኢትዮጵያ ተሰደዋል፡፡ ሰሞኑን የአንድ ኪሎ ቲማቲም ዋጋ 30 ብር መድረሱን፣ የአንድ ኪሎ ብርቱካን ዋጋ በሱፐር ማርኬቶች በትንሹ 64 ብር መሸጡን ታዝቤያለሁ፡፡ ከ10 ዓመት በፊት በኢትፍሩት የሽያጭ ኮንቴይነሮች ውስጥ በኪሎ አንድ ብር ሲሸጥ የነበረ ጣፋጭ ብርካን ዛሬ እንዲህ መሆኑ ይደንቃል፡፡ በዚህም ምክንያት ዘመድ ዘመዱን መጠየቅ አልቻለም፡፡ እየተቆራረጥን ነው፡፡ “ምን ይዤ ልሂድ” ከባድ ጥያቄ በሆነበት ማኅበራዊ ግንኙነታችን ላይ እንዲህ ያለ መብረቅ ሲወርድበት የሰዎች ተቆራርጦ መቅረት የሚጠበቅ ነው – በሦስት ብር ሁለት ኪሎ ሙዝ ይዞ መሄድ ዱሮ በደጉ ዘመን ቀረ – ዛሬ ለሁለት ኪሎ ሙዝ በትንሹ 40 ብር ያስፈልግሃል፡፡ ኑሮ እንደባንዴራ በቅርብ መሰቀሉን ትታ እንደመንኮራኩር ተተኩሳለች፡፡ ይቺ የስሙኒ ደመወዝ ደግሞ ከፍ ሲል እንደጠቆምኩት ከልደታ እስከባታ የዳቦ መግዣ ከመሆን አላለፈችም፡፡ ምን ይዋጠን? ማን ይድረስልን? እግዚሃሩን ማን አገተብን? “ተዛዘኑ፣ ተሳሰቡ፣ አንዱ በሌላው አይጨክን፣ ወንድም ለወንድሙ ይራራ” የሚለውን ሃይማኖታችንን አጥፍቶ ሆድ አምላኪነትን የተከለብን ማን ይሆን? የኑሮ ውድነቱን በተመለከተ ብናወራው አያልቅም፡፡ የገንዘባችን የመግዛት አቅም ከቀደምት ደጋግ ዘመናት ጋር ሲነጻጸር በቀላል ግምት የዱሮዎቹ አንድ ብሮች የአሁኖቹን ከ500 እስከ 1,000 ብር ይመነዝራሉ ቢባል ጨዋነትን የተላበሰ በጣም አነስተኛ ግምት ነው፡፡ የ35 ሣንቲም ቢራ አሁን በአማካይ (አንዲት ቡትሌ ቢራ በመቶዎች የሚሸጡባቸውን እነ ሸራተንንና ሂልተንን እንዲሁም አንዳንድ ዝጉብኞችን ትተን) 16 ብር ሲሸጥ፣ የ30 ሣንቲም ስኳር አሁን 22 ብር ሲሸጥ፣ የአምስት ሣንቲም 20 መርፌዎች አሁን ሃያ ብር ሲሸጥ፣ የ30 ብር ማኛ ጤፍ አሁን 2,500 ብር ሲሸጥ፣ የስሙኒ የሥጋ ወጥ ምሣ አሁን በአማካይ 60 ብር ሲሸጥ… መቶኛ የዋጋ ንረቱን ለማወቅ የስልክህን ካልኩሌተር አውጣና ምታው፡፡ የደም ብዛትህን ግን ተቆጣጠር፡፡ ካንተ እሚብስ የለም ልጄ፤ ለነገ እንድትደርስ ጠንቀቅ በል፤ “ነገም ሌላ ቀን ነው” ይባላልና፡፡ በዚህ ላይ በሰሞኑ የገባብን የኮሌራ ወረርሽኝ ደግሞ ውዶቻችንን ከጉያችን እየሞጨለፈብን ነው፡፡ መንግሥት የሌለው ሕዝብ አሣሩ ብዙ ነው፡፡ እንደሚባለው የቆሻሻ ፍሳሽና የመጠጥ ውኃ መስመሮች ሳይቀላቀሉ አይቀሩም፡፡ ዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ፡፡ ዱሮውንም የኛ የቧንቧ ውኃ ለአውሮፓውያን እንስሳትም አይመከርም ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ለይቶልን የሸናነውን አዙረን ልንጠጣውና በአተት በተመካኘ ኮሌራ ልናልቅ ተፈርዶብናል፡፡ ችግራችንን ዘርዝረን አንጨርሰውም፡፡ እሱው ይሁነን፡፡ ግን እንጸልይ፡፡ በቃ፡፡ እንደ ዶፍ እየወረደብን ያለው ወያኔያዊ ግፍና በደል ዕፁብ ድንቅ ተዓምራትን ባካተተ መለኮታዊ ኃይልም ጭምር እንጂ በሰብኣዊ ኃይልና ጥበብ ብቻ የሚወገድ አይመስልምና በርትተን ፈጣሪን በጸሎት/በዱዓ እንለምነው፡፡ የገባንበት የመከራ አዘቅትና የምንዳክርበት አዙሪታዊ ማጥ… በቃላት የሚገለጽ አይደለም – ለመረዳት እንኳን እንደኛ በውስጡ መኖርን ይጠይቃል፡፡ ይህን መሰሉን ለጆሮ የሚቀፍ ችግር ለወዳጅ አይደለም ለጠላትም አይስጥ፡፡ መንጋቱ ግን አይቀርም፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s