አረብ እስፕሪንግ የአረብ ዊንተር ሲሆን (መስቀሉ አየለ)

መስቀሉ አየለ

አረቦች ሲባሉ የሰብእና እና የእውቀት መካን መሆናቸውን ይኽ ዘመን ምስክር ሆኗል።ዛሬ ሃገራቸው እንደ አሹቅ ባቄላ መንፈር የያዘባቸው የአረብ አይምሮ ዘገምተኛ መሪዎች በያዝነው አመት ውስጥ “የዱባይ ኮንቬንሽን” የተባለ ጉባኤ ለማካሄድ ደፋ ቀና እያሉ ሲሆን ተሰናባቾቹ ባንኪሙንና ባራክ ኦባማ የክብር ተናጋሪዎች ዝርዝር ውስጥ በመግባታቸው ለሚያደርጉት የጥቂት ሰዓታት ንግጝር በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ቸክ ተቆርጦላቸዋል። ክፍያ መሆኑ ነው። ነገር ግን የአካባቢው ጂኦፖለቲክስ ሁኔታ ልቃቂቱ እንዲህ በቀላሉ የሚገኝ አይደለምና ከዚህ ጉባኤ ጠብ የሚል ነገር እንደሌለ አዘጋጆቹም ሰይጣንም ያውቁታል። ዘመናዊው የአረብ አገሮች አከላለል የአስራ ዘጠነኛው ምእተ አመት የአውሮፓ ኮሎኒያሊስቶች ስሪት ነው። አረቦች አንድ ሆነውና ጠንክረው እንዳይወጡ እንግሊዝ ፈረንሳይና ጣሊያን መሬት የረገጠ ስራ ሰርተውበታል። ምንም እንኩዋን እስልምና እራሱን የቻለ አይዲዮሎጅ ሆኖ በመምጣት በኢስላሚክ ብራዘርሁድ አስተምህሮ “እስላም አገር የለውም” የሚል ማኒፌስቴሽን ለማስረጽ ቢሞክርም አረቦች ግን ዛሬም እንደ ተለያዩ ናቸው። በአንደኛውና በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት እንኩዋን በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአረብ ህዝቦች የፍጥጫው አካል ሆነው በማያውቁት ጦርነት ውስጥ ሁለት ጎራ ተከፍለው ደም ተቃብተዋል። የምእራቡ አለም በደም የጨቀዩ እጆች ዛሬ ከየመን እስከ ሶሪያ ሚሊዮኖች ወደ ሞት ሰረገላ እየተጋዙ ነው። የአምስት ሽህ አመታት እድሜ ያላቸው ከተሞች ወደ ትቢያነት ከመቀየራቸው የተነሳ የአርኪዮሎጅስቶች ንብረት ከመሆን የዘለለ ዋጋ ላይኖራቸው ይችላል። ልቃቂቱ በማይታወቅና መጨረሻ በሌለው ጦርነት ውስጥ እንደ መዘፈቃቸው አንዳቸውም የአረብ አገር መሪም ሆነ የወታደራዊ ባለሙያ ከዚህ ጦርነት ጅማሮ የምእራባውያንን እርዳታ የጠየቁበት አጋጣሚ የሌለ ቢሆንም ጦርነቱን ማቆም ቀርቶ በመፍትሄ ፍለጋው ዙሪያ በጥርስ አልባው የተባበሩት መንግስታትንም ሆነ የጸጥታውን ምክር ቤት ትብብር ሲጠይቁ መፍትሄ ቀርቶ አጀንዳ አስይዞ ወደ መድረክ ለማምጣት እንኩዋን ሳይቀር የነጮቹን ደጅ መጽናት እራሱን የቻለ ህመም ሆኖዋል። ምእራባውያን እንዲህ ያለ የደም መሬት ለመፍጠር እንቅልፍ ያጡበት ዋናውም ባይሆን አንዱ መሰረታዊ ምክንያት ግን ቀደም ባለው የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን ለመሳሪያ ሽያጭ የሶቪየት ኤምፓየር አይዲዮሎጅና የአለም በሁለት ንፍቀ ክበብ መከፈል ዋነኛው ማሳበቢያ የነበረ ሲሆን ዛሬ ደግሞ ያ የቀድሞ ምክንያት ባለመኖሩ እግር ተወርች የተያዘው የምእራባውያን የጦር መሳሪያ ፋብሪካዎች ምርት የወገቡ ማረፊያ የማግኘቱ ጉዳይ የግድ የመሆኑ ነገር ነው።በዚህም የተነሳ የአርብ ስፕሪንግን ተከትሎ ዛሬ ዙሪያን በሚንፈቀፈቀው የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ለመሳሪያ ሽያጩ የሰማያት ደጅ መከፈቱና ቀጣይነት ባለው መልኩ ለምእራብ መንግስትታ የማያቁዋርጥ የገባያ ሜዳ ለመፍጠር ሲባል መቸም ሊቆም የማይችል የጦርነት አዙሪት ውስጥ ማስገባትን የግድ አድርጎታል። ዛሬ በሺያትና በሱኒ መካከል የተለኮሰው እሳት እኒህ ሁለት የሃይማኖት አስተምህሮዎች ለአስራ ስድስት መቶ አመታት በሰላም ተጋብተውና ተዋልደው ብሎም ማህበረሰብም አገርም ሆነው የኖሩ የማይመስልበት አደገኛ የጥላቻ ሰርጥ ውስጥ መዘፈቃቸው ይህ ነገር ለመሳሪያ ነጋዴዎቹ ገበያውን የቄጠማ ላይ ጉዝጓዝ አድርጎላቸዋል።ነገሩን ከድጡ ወደማጡ የሚያደርገው መራራው እውነት ደግሞ ወዲህ ነው፤ይኸውም አረቦቹ ወደ ዚህ ጦርነት ውስጥ እንዴት ገብተው እንደቀሩ አለማወቃቸውና ብሎም ምን እየተካሄደ እንደሆነ ለመገምገም የሚያስችል ትንታኔ መስጠት የሚችል ፕሮፌሽናል ተቁዋም አለመኖሩ ሲሆን በአንጻሩ ግን የምእራብ መንግስትታ ከደራው ገበያም በላይ የእብድ ገላጋይ በመሆን የመካከለኛውን ምስራቅ ወደ ትቢያነት የመቀየሩን ዘመቻ በሰፊውና በተጠና መንገድ አጠንክረው የመግፋታቸው ነገር ነው። እንደ ምሳሌ “እንኩዋን ብንወስድ ጋዳፊን ለመደብደብ ያወጣሁት ነው” በሚል በጋዳፊ ስም በኒዮርክ ተቀምጦ የነበረውን አምሳ ቢሊዮን ዶላር ውሃ በልቶታል። ባለፈው አመት የካሜሮን አስተዳደር ለየመን ስለሰጠው የአስቸኩዋይ ግዜ እርዳታ በኩራት ሲናገር አንድ ደሙ የፈላ አንድ የፓርላማ አባል “ስለ 30 ሚሊዮን ብር እርዳታ ከምታወራ በአለም አቀፍ ደረጃ የተከለከሉትን ክላስተር ቦምቦች ጨምሮ ለሳውዲ አረቢያ የሸጥከውን የ12 ቢሊዮን ፓውንድ የጦር መሳሪያ ዝርዝር ለምን አትነግረንም” ነበር ማለቱ ተጠቅሷል።ከላይ በክላስተር ቦምብ ንጹሃንን ሲያስቀጥፍና ከዚያም እንደ ሻይሎክ ገንዘብ ሲያተርፍ የሚውለው ካሜሮን ከታች ደግሞ ከእልቂቱ ተቆርጠው ለተረፉ ለጋ የየመን የህጻናት ገላ የቁስል ፕላስተር መግዣ የሚሆን መናኛ ሳንቲም ይወረውራል። ከምእተ አመት በፊት እንደ ነበረው በአርብ አገራት ውስጥ ግጭትን በማስወገድና መፍትሔ በማፈላለጉ በኩል ጥረቱ፣ ፍላጎቱ፣ ብልሃቱ፣ ልምዱና የሞራል የበላይነቱ የነበራቸው የተከበሩት የአገምር ሽማግሌዎቻቸውም ሆኑ ምሁራኑ እንዲህ አይነት የህዝብ ንቅናቄ ሲፈጠር አገሪቱን የሚያስተዳድሩትን አካላትም ሆነ ህዝቡ ላይ ተጽእኖ ፈጣሪ የሆኑትን ወይንም የንቅናቄው አካላትን ሁሉ መስመር በማስያዝ ችግሩን በቀላሉ የማብረድ ሚና መጫወት ይችሉ ነበር። እንዲህ አይነት ሰዎች ዛሬ ተገፍተው በመውጣታቸውና አዲስ እየመጣ ያለው ጽንፈኛ ትውልድ ነገሩን ሁሉ በሃይል ለመለወጥ ይዞት የመጣው የጉልበት አካሄድ የገዛ ምድራቸውን ወደ ለየለት የምድር ገሃነም እያደረገው ነው። ዛሬ በሶሪያ በሊቢያ በየመንና በመሳሰሉት አገሮች የሚታየው እብደት ከዚህ የወጣ አይደለም። ከጥቂት ወራት በፊት አንድ የግራ ዘመም መጽሄት እንዲህ ብሎ መጻፉን አንብቤያለሁ “Arabs by Nature appear allergic to rational thinking and remedial solutions. Not so, across the bloody centers of humanitarian catastrophes at Aleppo, Damascus, Sana and elsewhere, Arab wisdom and new creative initiatives are missing as if they breathe in a dead-ended corner of moral and intellectual abyss. Consequently, Arab people are fast becoming victims of their own pitfalls of self-destruction” ቀጥዩ የኢትዮጵያ ጣጣ ኢትዮጵያ እንደ አገር ካርታዋ ያለው በአፍሪካ ቀንድ ላይ ቢሆንም በሽዎች አመታት በሚቆጠረው እረጅሙ ታሪኳ ውስጥ ግን እስከ አስራ ዘጠኝ መቶ ስልሳዎቹ ድረስ ከጎረቤት ኬንያ ይልቅ የመካከለኛው ምስራቅ፤ እስራኤልና ፔርሽያንስ አካል ሆኖ እንደቆየች የቋንቋዋንና የባህል ግንኙነቷን ማየት ይቻላል። ለዚህ ደግሞ የቀይባህርን ትራስ አባይን መቀነት አድርጋ መኖሯ ዋነኛው ምክኛት ሊሆን ይችላል። በዚህም የተነሳ በመጥፎውም ሆነ በጥሩው በዚህ የመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ የሚፈጠር ማንኛውም አይነት ነገር በአገራችን ላይ የሚኖረው ተጽእኖ ቀላል አይደለም። ዛሬ ለስድስት አመት የቆየው የሶሪያ ጦርነት የሃይል አሰላለፉን ቀይሮ ወደ ቀይባህና የደቡብ ሱዳን ሰርጥ ውስጥ መግባት መጀመሩን እያየን ነው። ከጥቂት አስርተ አመታት በፊት ዘላን የነበሩ የግመል ጠባቂዎች ዛሬ ኤምሬቶች ተብለው በሰሜን ሶማሊያ የወታደራዊ ካምፕ ገንብተዋል። የመንን ከምስራቅ አውሮፓና ከላቲን አሜሪካ በተገዙ መርሰነሪ ፓይለቶች ቀን ከሌት ያሰደበድባሉ። የአሜሪካን መንግስት ባልተለመደ ሁኔታ ለብዙ አስርተ አመታት ጠላት አድርጎት የቆየውን የአልበሽርን መንግስት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የጣለውን ማእቀብ ድንገት ለማንሳት እስከ መገደድ የደረሰበት ሁኔታ ግልጽ አይደለም። ይልቁንም አሁን እየወጣ ያለው ዘገባ እንደሚያመለክተው ከተቻለ በሱዳን በኩል የተሻለ ተጽእኖ ፈጣሪ ሊሆን ይችላል የሚባለው ለዘብተኛው፣ የኦክስፎርድ ተማሪውና አዛውንቱ ሳዲቅ አልማሕዲ እንዲረከብና አልበሽርም ያለ ተጠያቁነት በሰላም እንዲኖር ነው የሚጎነነጎነው። ግብጽ የደቡብ ሱዳንን የአውሮፕላን ጣቢያ ጀምሮ የወታደራዊ ተቁዋም መገንባቱ ላይ ተጠምዳለች። ኩዋታርና ሳውዲ አረቢያ ጅቡቲ ደርሰዋል። አሰብን በተመለከተ የሚወራው ብዙ ነው። ይህንን ሁሉ ስናየው መንግስት አልባዋ ኢትዮጵያ በሁሉም አቅጣጫ መከበቧ ግልጽ እየሆነ ነው። በዚያ ላይ አረቦች በቀይ ባንብረቱም ጭምር ሳይወረስ በዛው በካርቱምአካባቢ መሰረት መጣላቸው እስከ ዛሬ ድረስ ከእስላማዊ ጽንፈኝነት ጸድቶ የነበረውን የአፋሩ ማህበረሰባችን የአረቦች ሰይጣናዊ አይዲዮሎጅ ሰለባ ሊያደርገው አይችልም ማለት አይደለም። ስለዚህ እኛ ኢትዮጵያውያውያን ከጎጣችን ተሻግረን ዙሪያ ገባውን በማየት እንደ ህብረተሰብ አንድ ሆኖ ጠንክሮ ከመቆም ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለን ለማየት ብዙ የረፈደብን አይመስለኝም።

Leave a comment